የኢሜግሬሽን እና ዜግነት ጉዳዮች ኤጀንሲ በአራት ወራት ውስጥ ሦስት ሺ ፓስፖርቶች መባከናቸውን ገለጸ
በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት 200 ሺ ፓስፖርቶችን ለዜጎች ማሰራጨት ቢቻልም፤ ሦስት ሺ አገልግሎቱን ጠያቂ ግለሰቦች የተዘጋጀላቸውን ፓስፖርት ቀርበው ባለመረከባቸው ሊባክን መቻሉን የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ገለጸ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጅብ ጀማል በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኤጀንሲው በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት 200 ሺ ፓስፖርቶችን በአስቸኳይና በመደበኛ ክፍያ አገልግሎቱን ለጠየቁ ዜጎች ያሰራጨ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ከመስከረም እስከ ታህሳስ ወር ለዜጎች ከተሰራጩት 150 ሺ ፓስፖርቶች ውስጥ ሦስት ሺዎቹ ፓስፖርታቸውን ባለመውሰዳቸው ባክኗል።

አገልግሎት ጠያቂዎቹ በፖስታ ሳጥን ቁጥር አድራሻቸው ፓስፖርታቸው ቢላክም ሳይወስዱ ሦስት ወር በመሙላቱ ለኤጀንሲው ተመላሽ በመደረጉ ኤጀንሲው የአገርና የወገን ሀብት እንዳይባክን በስልክ አድራሻቸው ደውሎ እንዲወስዱ ጥሪ ቢያስተላልፍም አብዛኞቹ ፓስፖርቱን እንደማይፈልጉት፤ አንዳንዶች ደግሞ ስነምግባር የጎደለው ምላሽ መስጠታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ሦስት ሺ አገልግሎት ጠያቂዎች ለፓስፖርት ማውጫ የሚጠየቀውን ገንዘብ ከፍለውና በቀጠሮ ጊዜያቸውን አባክነው ጥቅም ላይ ሳያውሉት በመቅረቱ ገንዘብ ባክኗል። ሌሎች ሊጠቀሙበት የሚችሉበትን እድል አሳጥተዋል። ስለዚህ ህብረተሰቡ ለጉዞ ሲዘጋጅ፣ የጉዞ እቅድ ሲኖረው፣ የሚሄድበትን ቀን አስቦ እና አቅዶ ፓስፖርቱን መውሰድ ይገባል። እንደ አገርና እንደ ግለሰብ ኪሳራን ይቀንሳል። እንዲሁም በጊዜው አገልግሎቱን ማግኘት የሚገባቸው ዜጎች እድሉን እንዲያገኙ በር ይከፍታል።

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ፓስፖርት በአስቸኳይ ከአንድ ቀን እስከ አምስት ቀን እንዲሁም በመደበኛ እስከ 75 ቀን በቀጠሮ ማግኘት እንደሚችል የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኤጀንሲው ባጋጠመው የፓስፖርት ክምችት እጥረት ከመጋቢት እስከ ነሐሴ 2011 ዓ.ም ድረስ አስቸኳይ ምክንያት ላላቸው ዜጎች ብቻ ፓስፖርት ይሰጥ እንደነበር ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ኤጀንሲው የተሳሳተ መረጃ ይዘው የሚቀርቡ ዜጎችን ለህግ አሳልፎ በመስጠት ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዜጎች ባቀረቡት ማስረጃ መሰረት የተስተናገዱ ቢሆንም በመካከል ሀሰተኛ ማስረጃን እያቀረቡ ስራውን የሚያስተጓጉሉ በቀን ሁለትና ሦሰት ሰዎች እንደሚያጋጥሙ ጠቁመዋል ።

ዋና ዳይሬክተሩ ከነሐሴ 2011 ዓ.ም በኋላ የፓስፖርት እጥረቱ በተወሰነ መልኩ በመቀረፉ አስቸኳይ ፓስፓርት ከሚወስዱ ዜጎች ባሻገር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፓስፖርት የመውሰድ መብት ስላለው በመደበኛው በ60 ቀን ወይም በሁለት ወር ቀጠሮ እንዲወስዱ መደረጉን ገልጸዋል።

በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በወር ከአምስት እስከ 10 ሺ ፓስፖርቶች ታትመው ወዳሉበት አገራት እንደሚላኩና በአገር ውስጥ ላሉ ዜጎች በቀን እስከ ሦስት ሺ ፓስፖርቶች እንደሚታተም ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ ፓስፖርቱ ሰዎች ወደ ተለያዩ አገሮች ሲጓዙ እንዲገለገሉበት ተብሎ የሚሰጥ የጉዞ ሰነድ በመሆኑ ለጉዞ የተዘጋጀ ወይም እቅድ ያለው ብቻ መውሰድ እንዳለበት አመልክተዋል።

ኤጀንሲው ለሁሉም ዜጎች ፓስፖርት እየሰጠ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፤ አንድ ሰው በመደበኛ በ75 ቀን ቀጠሮ በ600 ብር፣ አስቸኳይ ፓስፖርት የሚፈልግ ከሆነ ደግሞ ህጋዊ ማስረጃ በማቅረብና ምክንያቱን በመግለጽ በሦስት ሺ 200 ብር በአንድ ቀን ߹ሁለት ሺ 200 ብር ከፍሎ ደግሞ ከአምስት ቀን በታች መውሰድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በኤጀንሲው እስከ መጋቢትና ሚያዚያ መጨረሻ 170 ሺ ዜጎች በመደበኛው ጊዜ ፓስፖርት ለማግኘት ተቀጥረው እየተጠባበቁ ሲሆን ፤ ለወደፊትም የፓስፖርት እጥረቱን በመቅረፍና ተደራሽነቱን በማስፋት በዓለም ዓቀፍ መስፈርት ቢያንስ በሦስት ሳምንትና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱ የሚሰጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።

Embassy's Address


 Embassy Address:

1501-275 Slater Street, Ottawa Ontario
K1P 5H9 Canada 

Tel (613) 565 6637 / Fax (613) 565 9175

 Email: info@ethioembassycanada.org  

For consular services

Email: consular@ethioembassycanada.org


 

JSN Gruve is designed by JoomlaShine.com